Admin2
Sat, 11/22/2025 - 21:00
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የህብረተሰቡን እርካታ ያረጋገጠ መሆኑ ተጠቆመ። (ህዳር 13/2018) 20ኛውን የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ምክንያት በማድረግ ከመላው ሀገሪቱ የተውጣጡ የጋዜጠኞች ቡድን አባላት በሆሳዕና ከተማ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የስራ እንቅስቃሴ ተመልክተዋል። የአገልግሎቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ከበደ ሻሜቦ እንደገለጹት በክልሉ ተገንብቶ ስራ የጀመረው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ፈጣን፣ ቀልጣፋ፣ ጊዜና ገንዘብ ቆጣቢ አሰራርን መሰረት ያደረገ ነው ብለዋል። በማዕከሉ በ7 ተቋማት 20 አገልግሎት እየተሰጠ ነው ያሉት ስራ አስኪያጁ በዚህም የህብረተሰቡን እርካታ ማረጋገጥ አስችሏል። በማዕከሉ 1ሺ 948 ተገልጋይ ተጠቃሚ ስለመሆናቸውም ስራ አስኪያጁ አመላክተዋል። የተገልጋዩን መረጃ በቴክኖሎጂ የተደገፈ እንዲሆን አስችሏል ያሉት ስራ አስኪያጁ ወደፊት 60 አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ማዕከል መሆኑንም ጠቁመዋል። መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር )መስከረም 15/2018 ተመርቆ ወደ ስራ መግባቱ ይታወሳል።