Skip to main content
zena75

በክልሉ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ በተሰጠው የተግባር ስልጠና በቂ እውቀትና ክህሎት ማግኘት መቻላቸውን ሰልጣኞ ተናገሩ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ለስምንት ተከታታይ ቀናት በወራቤ ከተማ ሲሰጥ የነበረው የአሰልጣኞች ስልጠና ተጠናቋል። በቢሮ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ልማትና አስተዳደር ዘርፍ ኃላፊ አቶ ከበደ ሻሜቦ እንደገለፁት ስልጠናው በየተቋማቱ አገልግሎት ላይ የሚዉለዉ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሳሪያዎች ላይ ያተኮረ አድቫንስድ ኦፊስ ማሽን የተግባር ስልጠና እንደነበረ ተናግረዋል። በየተቋሙ የሚሰጡ አገልግሎቶች በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መታገዝ ያስፈልጋል ያሉት አቶ ከበደ ለዚህም የዘርፉን የሰው ሀይልን በቴክኒካል ክህሎት ማስታጠቅና ማብቃት ተገቢ ነው ብለዋል። ስልጠናው የአስልጣኞች ስልጠና እንደመሆኑ መጠን ለተቋማት የሚያስፈልጉ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሳሪያዎች እንዳይበላሹ አስቀድሞ መከላከልና ሲባላሽም ለመጠገን የሚያስችል ስልጠና ነው ብለው የአገልግሎት መሳሪያዎቹ ሲገዙ ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆን በእውቀት ላይ የተመሰረተ ግዢ ለመፈጸም የሚረዳ በመሆኑ ሰልጣኞች ያገኙትን እውቀትና ክህሎት ወደየመጡበት ተቋማት ላይ መተግበር ያስፈልጋል ሲሉም ተናግረዋል። ሰልጣኞቹም ከክልሉ ሴክተር መ/ቤቶች፣ ከዞን እና ከልዩ ወረዳ የተወጣጡ መሆናቸውን የገለፁት አቶ ከበደ ስልጠናው በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። ሰልጣኞቹ እንደተናገሩት በተሰጠው የተግባር ስልጠና በቂ እውቀትና ክህሎት ማግኘት መቻላቸውን ገልፀው በየተቋማቱ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ የሚፈጠረው ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችል እንደሆነ ተናግረዋል። በየተቋማቱ በቀላሉ ሊስተካከሉ የሚችሉ ነገር ግን በዘርፉ በቂ እውቀት ከላመኖሩ የተነሳ የሚጣሉ እና የሚባክነውን የመንግስት ንብረትን በቀላሉ ለማዳን ብሎም ወጪን ለመቆጠብ የሚያስችል ስልጠና ነው ብለው በቀጣይ ሌሎችን በማሰልጠን ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ገልፀዋል። የመደረኩ አሰልጣኝ የነበሩት ኢያሱ ጌታቸው እንደገለፁት ሰልጣኞቹ በቀጣይ በየተቋማቱ በትንሽ ብልሽት የቆሙ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን በመጠገን አገልግሎት ላይ ለማዋል የሚረዳ እውቀት መቅሰማቸውን ገልፀው ድርጅቱ በሰልጣኞች እውቀት ሽግግር ላይ አበክሮ እየሰራ ስለመሆኑም ጠቁመዋል።