Skip to main content
zena74

መሶብ-የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዲጂታል ሲቪል ሰርቪስን በመገንባት ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠትና ብልሹ አሠራርን ለመከላከል ፋይዳው የላቀ መሆኑን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ገለጸ። ለማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት አመራሮችና ባለሙያዎች የተዘጋጀ የአቅም ግንባታ ስልጠና በሆሳዕና ከተማ ተሰጥቷል። የአገልግሎቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ከበደ ሻሜቦ እንደገለጹት መሶብ-የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዲጂታል ሲቪል ሰርቪስን በመገንባት ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠትና ብልሹ አሠራርን ለመከላከል ፋይዳው የላቀ ነው። ለዚህም አገልግሎትን በመሶብ ስታንዳርድ መስጠት የሚያስችል አቅም ለመገንባት ታልሞ ስልጠናው መዘጋጀቱን አቶ ከበደ ጠቁመዋል። መሶብ-የአንድ ማዕከል አገልግሎት በአደረጃጀት፣ በአሠራርና በአመለካከት የሚፈጥረውን ምቹ ሁኔታ ተጠቅሞ የተገልጋይ እርካታን ማሳደግ ከስልጠናው የሚጠበቅ ውጤት መሆኑንም ሥራ አስኪያጁ አስገንዝበዋል። ስልጠናው በመሶብ-የአንድ ማዕከል አገልግሎት የሥነ-ምግባር እሴት ግንባታ እና ስታንዳርድ ላይ ያተኮረ ሲሆን በመርሃ-ግብሩም በሰነድ የተደገፈ ገለጻ ተሰጥቶ ሰፊ ውይይት ተደርጓል። የሥነ-ምግባር እሴት ጥቅል ዕይታ፣ የሥራ ምንነትና የሥራ መሪዎች ሥነ-ምግባርን የሚያሰፍኑባቸው መንገዶች፣ የሥራ ሥነ-ምግባር እሴት የአገልግሎት አሰጣጥና ስታንዳርድ ትስስር በሚሉ ንዑስ ርዕሶች ላይ ተሞክሮና ገለጻ ቀርቦ የውይይት ማጠቃለያ ተደርጓል። የስልጠናው ተሳታፊዎችም ስለአገልጋይ-ተገልጋይ መስተጋብርና መርሆዎቹ፣ ስለሥነ-ምግባር፣ ስለተቋማዊ እሴቶች ግንዛቤ መጨበጣቸውን ገልጸው በቀጣይ የክህሎትና የአመለካከት ብቃታቸውን ለማሻሻል ስልጠናው ጉልህ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል። በማዕከሉ የሰው ኃይል አቅም ለማጎልበት ዘርፈ-ብዙ ተግባራት እየተፈጸሙ ሲሆን በቀጣይ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ክህሎት ለማሳደግ ያለመ ስልጠና ለመስጠት መታቀዱም ተገልጿል። በዕለቱ መርሃ-ግብር በማዕከሉ ለምቶ ለአገልግሎት የተዘጋጀ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ፖርታል አጠቃቀም በተመለከተ ለአገልግሎት ሰጪዎች ገለጻ ተሰጥቷል።