የክህሎት ማጎልበቻ ስልጠና ለባለሙያዎች እየሰጠ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ አስታወቀ! ወራቤ፤ጥቅምት 19/2018 ስልጤ ኤፍ ኤም ስልጠናውን አስመልክቶ ከስልጤ ኤፍ ኤም ቆይታ ያደረጉት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ከበደ ሻሜቦ በክልሉ የሚገኙ የቴክኖሎጂ ባለሙያዎችን ቴክኒካል ክህሎት ማጎልበቻ ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን አስታውቀዋል ። የስልጠናው ዓላማ በክልሉ በተለያዩ ምክንያቶች ከአገልግሎት ውጭ የሆኑ ማሽኖችን ጠግኖ ወደ ስራ ለማስገባት መሆኑን የገለፁት አቶ ከበደ ለ12 ተከታታይ ቀናት በተግባር እንደሚሰጥም ተናግረዋል ። ስልጠናው በካምፓኒ ደረጃ የሚሰጥ መሆኑን በመግለፅ በሁሉም መዋቅሮች አገልግሎት የማይሰጡ ኮምፕዩተሮችን ፣ታብሌቶችን፣ የፎቶ ኮፒ ማሽኖችን ፣ ስካነሮችን ፣ ፕሮጀክተሮችን እና ማባዣ ማሽኖችን ለመጠገን ታሳቢ ያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል ። ስልጠናው በሚሰጥበት ማዕከል የሚገኙ የተበላሹ ማሽኖችን በመጠገን በተግባር የሚታገዝ ሲሆን ከስልጠናው በኃላ በየደረጃው ቲም ተዋቅሮ በሁሉም ተቋማት የሚገኙ ማሽኖችን የመጠገን ስራ ይሰራል ብለዋል። ለስልጠናው በቂ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የገለፁት አቶ ከበደ ከክልል ቢሮዎች ፣ ከዞንና ልዩ ወረዳ መዋቅሮች የተውጣጡ ከ30 በላይ ባለሙያዎች በስልጠናው ተሳታፊ መሆናቸውንም ገልፀዋል ። በስልጠናው የቴክኖሎጂ እቃዎችን አጠቃቀም እና አያያዝ በተመለከተ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ እንደሚሰራም ተገልጿል ።