CebositAdmin
Wed, 09/24/2025 - 09:42
የሀገር በቀል እውቀት፣ ቴክኖሎጂና ምርምር ፖርታል እየለማ እንደሆነ ተገለፀ፡፡ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እየለማ ባለው ፖርታል ላይ ከባለድርሻ አካላት ግብዓት የማሰባሰብ መድረክ ተካሂዷል፡፡ መድረኩ በውስጥ አቅም የለማውን የሀገር በቀል እውቀት፣ ቴክኖሎጂና ምርምር ፖርታል ይበልጥ ለማጎልበት ግብዓት ለማሰባሰብ ያለመ ነው፡፡ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የቴክኖሎጂ ልማትና ሽግግር መሪ ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር ተክለማርያም ተሰማ ኢትዮጵያ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን መረጃዎችን ለአለም አቀፍ ግብዓት በሚሆን መልኩ በማደራጀት ፖርታል ላይ ለማስቀመጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ የአንድ ሀገር ዳታ ለሁለንተናዊ አለም አቀፍ ጠቀሜታ ፋይዳው የላቀ ነው ያሉት መሪ ስራ አስፈፃሚው ሀገራችን በሁሉም ዘርፍ በአለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንድትሆን የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዳታ ቤዝ ወሳኝ ሚና እንዳለው ገልፀዋል፡፡ ፖርታሉ ኢትዮጵያ ያላትን የሀገር በቀል እውቀት ለአለም አቀፍ ማህበረሰብ ተደራሽ በማድረግ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል፡፡ በመድረኩ ተጠሪ ተቋማትና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት ሲሆን በቀጣይ የሚጠናቀቅበትን እድል በመፍጠር ወደ አገልግሎት እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡