
በጉራጌ ዞን የሚገኙ ወጣቶች በአዳዲስ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ስራ ላይ የተሻለ ክህሎት እንዳላቸውና ይህንን ወደ ውጤት በመቀየር የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላቶች በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ አስታወቀ። ጉራጌ ዞን የሳይንስ ፣የኢኖቬሽን እና የቴክኖሎጂ ማዕከል እናድርግ በሚል የዞኑ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ የ2017 በጀት አመት እቅድ አፈጻጸም ግምገማና የ2018 በጀት እቅድ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በወልቂጤ ከተማ የምክክር መድረክ አካሄዷል። በምክክር መድረኩ የተገኙ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ምክትል ሀላፊና የኢኮቴ ዘርፍ ሀላፊ አቶ ከበደ ሻሜቦ እንዳሉት በዞኑ የሚገኙ ወጣቶች አዳዲስ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ስራ ላይ የተሻለ ክህሎት እንዳላቸው አንስተው ይህን ንም ወደ ውጤት በመቀየር በዘርፉ የተሻለ ውጤት እንዲመጣ በቅንጅት መስራት ይገባል ብለዋል። የክልሉ ኢኮኖሚያዊ ፣ማህበራዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነትን ሊያጠናክሩና ሊያሳልጡ የሚችሉ የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማቶች ዝርጋታ ፣ በቴክኖሎጂ ልማትና አጠቃቀም ላይ የሰው ሃይል አቅም ግንባታ ስራዎች ላይ ብዙ መስራት የሚጠይቅ እንደሆነም አብራርተዋል። የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ እንዳሉት ተቋማት ቀልጣፋና ዉጤታማ አገልግሎት ለማህበረሰቡ ለመስጠት ቴክኖሎጂውን የበለጠ ማዘመን እንደሚገባም አመላክተዋል። ለነገ ምቹ መሰረት ለመጣል እየተሰሩ ያሉ ስራዎች አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ያመላከቱት አቶ አበራ በ2017 በጀት አመት አፈጻጸም ጠንካራ ጎኖችን በማስቀጠልና በጉድለት የታዩት ችግሮች ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባም አብራርተዋል። የጉራጌ ዞን ሳይንስና ኢንፎርሜሽ ቴክኖሎጂ መምሪያ ሀላፊ አቶ ደምስስ ገብሬ እንዳሉት የክልሉ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ በተቋማቸው ባዋቀረው የሲስተም አልሚ ቡድን አማካኝነት በርካታ ሲስተሞች ለማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቢሮዎች ማልማት እንደቻሉም አስታውሰው የጉራጌ ዞን አስተዳደርና የግብርና መምሪያ ህንጻዎች በኔትወርክ ዝርጋት በማስተሳሰር ረገድ የተሰራው ስራ ሁሉም ተቋማት ልምድ ሊወስድባቸውና ሊተገብራቸው እንደሚገባም አብራርተዋል። ፈጣንና አዳዲስ የቴክኖሎጂ መፍትሄዎችን በመዘርጋት ዞኑን ዲጂታላይዝ ለማድረግ የተጀመሩ ስራ7ዎች በቀጣይ የበለጠ አጠናክረው እንደሚሰሩበትም አስታውቀዋል። በመድረኩ የተገኙ አንዳንድ ባለ ድርሻ አካላት በሰጡት አስተያየት 2017 የስኬት ጊዜ እንደነበርና በሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ አበረታች ስራዎች የተሰሩበት እንደነበረ አስረድተው በቀጣይ የተሻለ ስራ ለመስራት ቅንጅታዊ አሰራሩን የበለጠ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም አመላክተዋል። በመጨረሻም በ2017 በጀት አመት የተሻለ ውጤት ላመጡ የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ፣የጉንችሬ ከተማ አስተዳደር የእዣ ወረዳ ፣የእኖር ወረዳ የሙሁርና አክሊል ወረዳዎች እንዲሁም ከመምሪያው ጋር በቅርበት ለሚሰሩ መምሪያዎች፣ ኮሌጆችና በመምሪያው የተሻለ አፈጻጸም ላመጡ ባለሙያተኞች የዋንጫ የሰርተፍኬትና የኮሚውተር ሽልማት አበርክቶላቸዋል። በተጨማሪም በኢትዮ ኮደርስ የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር፣ የእዣ ወረዳና፣ የጉመር ወረዳዎች የእውቅና ሽልማት እንደተበረከተላቸውና እንዲሁም ለእንደጋኝ ወረዳ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ጽህፈት ቤት የኮምፒውተር ድጋፍ ተደርጓል።