
የፈጠራ ስራ አውደ ርዕይዎች ወጣቶች እርስ በርስ እንዲማማሩ ጠቃሚ ልምድ የሚፈጥሩ ናቸው ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አንተነህ ፍቃዱ የፈጠራ ስራ አውደ ርዕይዎች ወጣቶች እርስ በርስ እንዲማማሩ ጠቃሚ ልምድ የሚፈጥሩ መሆናቸውን የማዕከላዊ ኢትዮዽያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፍቃዱ ተናግረዋል ። በክልሉ ''ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልልን የሳይንስ፣ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ማዕከል እናድርግ'' በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው ሁለተኛው ዙር የሳይንስና ፈጠራ ስራዎች አውደ ርዕይና ውድድር ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩን ጨምሮ በክልሉ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች ተጎብኝቷል። አቶ አንተነህ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ፈጠራ የማህበረሰብ ችግር መፍቻ ቁልፍ በመሆኑ የፈጠራ ስራዎችን ማሳደግ በፋይናንስና በቴክኒክ በመደገፍ ወደ አክሲዮን በመመስረት ወደ ኩባንያዎች እንዲሸጋገሩ መደገፍ ይገባል። የክልሉ ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ ሀላፊ አቶ ሙስጠፋ ኢሳ በፈጠራ ሳይንስና ፈጠራ ስራዎች የኢንተርፕራይዞች አስተማማኝ የስራ ዕድል ለመፍጠር እየተሰራ ነው ብለዋል። ቴክኖሎጂዎች ወደ ኢንተርፕራይዝ ተሸጋግረው ማህበረሰቡን እንዲጠቅም በማድረግ ቀጣይነት እንዲኖራቸው እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። የክልሉ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ሀላፊ አቶ ሰላሙ አማዶን እንደገለፅት የፈጠራ ስራዎች በህዝብ እንዲጎበኙ በማድረግ ፣ በማበረታታትና እውቅና በመስጠት ችግር ፈቺ የፈጠራና ምርምር ስራዎች ወደ ተግባር ተቀይረው ለክልላችን ብሎም ለሀገራችን ዕድገት አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ለማስቻል ነው ብለዋል። በአውደ ሪዕውና ውድድሩ ላይ ግብርና የሚያዘምኑ ፣ ለሚሊተሪ ሳይንስ እድገት የሚያግዙ ፣ ለኢንዱስትሪ እድገት አስተዋፅኦ የሚያበረክቱና ሌሎች በርካታ የፈጠራ ስራዎች ቀርበዋል።