
በዞን ደረጃ የተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎችን በማስጠገን ከ3 መቶ 5 ሺህ ብር በላይ የመንግስት ወጪ ማዳን መቻሉን የስልጤ ዞን ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ ገለጸ። ግንቦት 15/2017 በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ በኩል ከፍተኛ የሀርድዌር ጥገና ስልጠና ሲሰለጥኑ የቆዩ የዘርፉ ባለሙያዎች በስልጠናቸው ማጠናቀቂያ ከስልጤ ዞን የተለያዩ ተቋማት ተበላሽተው የተሰበሰቡ የኤሌክትሮኒክስ ቁሳቁሶችን በመጠገን ከ3 መቶ 5 ሺህ ብር በላይ የመንግስት ወጪ ማዳን መቻሉን የስልጤ ዞን ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ ገልጿል። የመምሪያው ሀላፊ ወ/ሮ ጀሚላ ሁሴን እንደገለጹት በተሰጠው የጥገና አገልግሎት በግዢ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁና በጥገና ደረጃም ከፍ ያለ ዋጋ የሚያስከፍሉ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን መሰሪያዎች ተጠግነዋል። በመምሪያ ደረጃ የኤሌክትሮኒክስ ቁሳቁሶችን የሀርድዌርና ሶፍትዌር ጤናማነት በማስጠበቅ ተግባራት በቴክኖሎጂ እንዲሳለጡ እየተሰራ መሆኑን ያነሱት ወ/ሮ ጀሚላ ዛሬ የተከናወነው የሀርድዌር ጥገና የተቋማቱን ወጪና ጊዜ ለመቆጠብ ትልቅ እገዛ እንዳለው አስረድተዋል። ዛሬ በተሰራው የጥገና ስራ የስልጤ ዞን ፋይናንስ ከተቋማት የሰበሰባቸውና ከስልጤ ዞን አስተዳደር የተሰበሰቡ ልዩ ልዩ ቁሳቁሶችን በመጠገን ከመንግስት ካዝና ሊወጣ የሚችል 3 መቶ 5 ሺህ ብር ማዳን መቻሉን ወ/ሮ ጀሚላ አስታውቀዋል። በዚህም መሰረት Richo mp 154,000 ብር፣ Color printer 14,000 ብር፣ Color printer 12,000፣ Printer 1300 45,000 ብር፣ Printer 4250 29,500፣ Fax machine 26,000፣ Hp 400 power supply 8,500 ብር እና Canon 2202 16,000 ብር በጥቅሉ 3 መቶ 5 ሺህ ብር ይከፈል የነበረ ወጪን ማስቀረት መቻሉን ወ/ሮ ጀሚላ አብራርተዋል። መምሪያው በቴክኖሎጂ መሳሪዎች ላይ የሚሰራውን የሀርድዌርና የሶፍትዌር ጥገና ስራ በማጠናከርና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም የአቅም ግምባታ ተግባራትን በማስቀጠል በዘርፉ ለተያዘው ግብ መሳካት የድርሻውን እንደሚወጣ ወ/ሮ ጀሚላ አስታውቀዋል። የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ጥገናውን በማሳለጥ ላበረከተው አስተዋጽኦና በተለያዩ መልኩ ለሚያደርጋቸው ያልተቋረጡ ድጋፎች ወ/ሮ ጀሚላ ሁሴን ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።