
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት 2ኛ ዙር ክልላዊ የሳይንስና የፈጠራ ሰራዎች ዐውደ- ርዕይ እና ውድድር ተከፈተ። በክልሉ እየተካሄደ የሚገኘውን የሳይንስና ፈጠራ ስራዎች አውደ ርዕይ እና ውድድር የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አንተነህ ፈቃዱ እና አፈ ጉባኤ ፋጤ ሰርሞሎ በወልቂጤ ከተማ መርቀው ከፍተዋል። የማዕከላዊ ኢትዮዽያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፍቃዱ በክልሉ በትምህርት ቤቶች ለሳይንስና ኢኖቬሽን ምቹ ከባቢ ለመፍጠር በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል። ዐውደ- ርዕይው ተማሪዎች፣ መምህራንና ኢንተርፕራይዞች ለሳይንስና ፈጠራ ስራዎች ያላቸውን ዝንባሌ በማሳደግ የተሻሉ የፈጠራ ስራዎችን ማበረታታትና ዕውቅና መስጠት፣ እርስበእርስ ልምድና ተሞክሯቸውን ኢንዲለዋወጡ ያስችላል ብለዋል። ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አክለው የፈጠራ ስራዎች በማህበረሰቡ እንዲጎበኙ በማድረግና የገበያ ትስስር በመፍጠር ወደ ተግባርና አገልግሎት በቀላሉ መቀየር የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል። የፌደራል፣የክልልና የዞን እንዲሁም የልዩ ወረዳ ከፍተኛ አመራሮች ዐውደ-ርዕዩን በመጎብኘት ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልልን የሳይንስ፣ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ማዕከል ማድረግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ የተለያዩ የፈጠራ ስራ ባለቤቶቾና ምሁራን በተገኙበት በፓናል ውይይት ይመክራሉ ብለዋል። የኢፌድሪ የሳይንስና ኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ድኤታ ዶ/ር በይሳ በዳዳ ቴክኖሎጂዎች የልማት ማፍጠኛ መሳሪያዎች ናቸው ብለዋል። የለውጡ መንግስት አካታችና ተደራሽ የሆነ የተሳሰረ የዲጅታል ኢኮኖሚ በመገንባት በርርካታ አገልግሎቶች ለዜጎች ተደራሽ ማድረግ ተችሏልም ብለዋል። በመርሃ ግብሩ የትምህርት ሚኒስቴር ዴኤታ ወይዘሮ አየለች እሸ ፣ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ሀላፊ አቶ ሰላሙ አማዶን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል። ''ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልልን የሳይንስ ፣ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ማዕከል እናድርግ!'' በሚል መሪ ቃል በተማሪዎች ፣በመምህራን ፣ በኢንተርፕራይዞችና በግል የተሰሩ ከ104 በላይ የሳይንስና የፈጠራ ሰራዎች ዐውደ ርዕይ እና ውድድር ለተከታታይ ሁለት ቀን ይቆያል። መድረኩ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ ከክልሉ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እና የስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ ጋር በጋራ የተዘጋጀ ነዉ።